የመልዕክት ርዕስ ፦ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ ዘፍጥረት 31 ፥ 16 ( ክፍል አንድ ) የመልዕክት ርዕስ አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ ዘፍጥረት 31 ፥ 16 ክፍል አንድ የተወደዳችሁ ቅዱሳን ወገኖች የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሙሉ ይህ የ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry አገልግሎት ነው በቅድሚያ እንኳን ጌታ እግዚአብሔር ለ2016 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ይህ ዓመት ለሁላችንም የበረከት የምስጋና የድልና ለእግዚአብሔር አገልግሎት መልካም የሥራ ዓመት እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ ለዕለቱ የሚሆን ዓመታዊ ጥቅስ በራሴና በ Joshua Breakthrough Renewal Teaching and Preaching Ministry ስም እንደሚከተለው ላቀርብላችሁ እወዳለሁ የዚህ ዓመት መሪ ጥቅሳችንም ከዚህ እንደሚከተለው ነው አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ ታድያ ይህ ጥቅስ ለያዕቆብ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ ላለነው ለኔና ለእናንተም በዚህ ዓመት እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ የምናደርግበት ዓመት ነውና በዚህ እውነት ውስጥ ሆነን ይህንን መልዕክት የምንሰማ ሁሉ እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ ለማድረግ በእምነት ልንነሳ ይገባል የላባ ልጆች ለያዕቆብ ያሉት ነገር ይህንን ነው ጊዜው አሁን ነው እያሉት ነው ምክንያቱም በአባታችን ቤት ለእኛ ድርሻና ርስት በውኑ ቀርቶልናልን ? እኛ በእርሱ ዘንድ እንደ ባዕድ የተቆጠርን አይደለንምን ? እርሱ እኛን ሸጦ ዋጋችንን በልቶአልና ስለዚህም እግዚአብሔር ከአባታችን የነሳው ይህ ሁሉ ሀብት ለእኛና ለልጆቻችን ነው አሁንም እግዚአብሔር ያለህን ሁሉ አድርግ ሲሉት እንመለከታለን ዘፍጥረት 31 ፥ 14 _ 16 ስለዚህ ያዕቆብ እግዚአብሔር ያለውን ለማድረግ በበቂ ሁኔታና ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተነሣ ሰው ነበር ወገኖቼ ሆይ ጌታ እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ ለማድረግ የተመቸ ጊዜና በቂ ሁኔታዎችን ዛሬም እርሱ እግዚአብሔር ይፈጥርልናል በመሆኑም እግዚአብሔር ያለንን እንዲሁ እንዲያው ዝም ብለንና ተነስተን ያለበቂ ሁኔታ ወይንም በሞቅታ መንፈስ የምናደርግ አይደለንም የሞላ ነገር ውስጥ ገብተንና ተረጋግተን እንደገናም እርግጠኞችም ሆነን የምናደርግ ነን ያዕቆብ በላባ ቤት በፍጻሜው እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ሊያደርግ የሞላ ነገር ውስጥ ገብቶ ነበር ይህን ያልኩበት ምክንያት ያዕቆብ ራሱ ከተናገረው ነገር ተነስቼ ነው አባታችሁ ግን አታለለኝ፥ ደመወዜንም አሥር ጊዜ ለወጠ፤ እግዚአብሔር ግን ክፉን ያደርግብኝ ዘንድ አልፈቀደለትም ደመወዝህ ዝንጕርጕሮች ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ዝንጕርጕሮችን ወለዱ፤ ሽመልመሌ መሳዮቹ ደመወዝህ ይሁኑ ቢለኝ በጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መሳዮችን ወለዱ እግዚአብሔርም የአባታችሁን በጎች ሁሉ ነሥቶ ለእኔ ሰጠኝ አለ ዘፍጥረት 31 ፥ 7 _ 9 ለዚህም ነው ሳይቸኳኮልና ጥድፍድፍም ሳይል በመነሳት ልጆቹንና ሚስቶቹንም በግመሎች ላይ አስቀምጦ መንጎቹንም ሁሉ የቤቱንም ዕቃ ሁሉ በሁለት ወንዞች መካከል ሳለ ያገኛቸውን ከብቶች ሁሉ ይዞ ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ወደ ከነዓን ምድር የሄደው ዘፍጥረት 31 ፥ 17 እና 18 መጽሐፍቅዱሳችን ሲናገር እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኰላ አትወጡም በመኰብለልም አትሄዱም አለን ኢሳይያስ 52 ፥ 12 በመሆኑም ያዕቆብን እግዚአብሔር የቀደመው በመሆኑ ምንም እንኳ ያዕቆብም የሶርያውን ሰው ላባን ከድቶ ኮበለለ መኮብለሉንም አልነገረውም ተብሎ የተጻፈ ቢሆንም እግዚአብሔር አድርግ ያለውን ሊያደርግ የተነሳ በመሆኑ በሕይወቱ ውስጥ በችኮላ መውጣት ድብብቆሽና የመኮብለልም ዓይነት ነገር አይታይበትም ነበር ለዚህም ነው ያዕቆብም ተቆጣ ላባንም ወቀሰው፤ ያዕቆብም መለሰ ላባንም እንዲህ አለው፦ የበደልሁህ በደል ምንድር ነው ? ኃጢአቴስ ምንድር ነው ይህን ያህል ያሳደድኸኝ ? አሁንም ዕቃዬን ሁሉ በረበርህ፤ ከቤትህስ ዕቃ ሁሉ ምን አገኘህ ? እነርሱ በእኛ በሁለታችን መካከል ይፈርዱ ዘንድ በወንድሞቼና በወንድሞችህ ፊት አቅርበው ሲል የተናገረው ዘፍጥረት 31 ፥ 36 ከዚህ ሃሳብ ተነስተን እንግዲህ ያዕቆብ ከዳተኛ ያልሆነና የፊት ለፊት የግንባርም ሰው የሆነ መሆኑን ከክፍሉ በዚህ መልኩ እንረዳለን አያይዞም ተነስቶም ወንዙን ተሻገረ ፊቱንም ወደ ገለዓድ ተራራ አቀና ይለናል ዘፍጥረት 31 ፥ 21 እግዚአብሔር አድርግ ያለውን ሁሉ ሊያደርግ የተነሣ ሰው ምንም ዓይነት ነገር ይሁን የቱንም ዓይነት ነገር ይምጣ መነሳቱ መሻገሩ ፊቱንም ሊሄድ ወዳሰበበት ሥፍራ ማቅናቱ የማይቀር ነው ይህን ለመሄድ የማቅናት ሁኔታን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስም በአንድ ሥፍራ አድርጎት ነበረ በሉቃስ ወንጌል 9 ፥ 51 _ 56 ላይ የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና በፊቱም መልዕክተኞችን ሰደደ ይለናል ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ ፊቱን በትክክል ያቀና ስለነበር በመንገዱ ላይ መጥተው ጥያቄ ላቀረቡለት ሰዎች ሁሉ ትክክለኛ መልስ ነበረው በመጨረሻም ማቅናቱ እውነተኛና የቁርጥ ስለነበረ ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለ ታድያ የያዕቆብም ሕይወት ካለበት ሁኔታ ተነስቶ ተሻግሮም በመሄድና በማቅናት ጉዳዩ ከዚህ የተለየ አልነበረም ወገኖቼ እንግዲህ እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ ለማድረግ ለተነሣን ለእኛም በእርግጥም እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ ለማድረግ ከተነሣን የሚታይብን ባሕርይ እና የጉዞ መጠን ይሄ ነው እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ ለማድረግ በፍጹም ሳንፈራ ተነስተን ልንሄድ እንደ ያዕቆብ መሻገር የሚገባንን ሁሉ እንሻገራልን መሄድ ወደ ተገባንም ሥፍራ ፊታችንንም እናቀናለን ለጠያቂዎቻችንም የምንሰጠው መልስ እንደ ኢየሱስ ማመንታትም ሆነ ወደኋላ ማለት የሌለበት መልስ ነው ታድያ ወገኖቼ አሁኑም እግዚአብሔር ያለንን ሁሉ ለማድረግ በእነዚህ እውነቶች ሁሉ ይጎብኘን ከዚህ በመቀጠል በቪዲዮ በፓወር ፖይንት መልክ ተዘጋጅቶ የቀረበ መልዕክት ስላለ ይህንን መልዕክት እንድትከታተሉ በጌታ ፍቅር ለማሳሰብ እወዳለሁ አዲሱ ዓመት ለሁላችንም የበረከትና የሰላም ዓመት ይሁንልን ጌታ እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይባርክ በማለት የምሰናበታችሁ ቀሲስ ዮናስ ጌታነህ ነኝ

Comments

Popular posts from this blog

የጌታ እራት ዛሬ ለእኛ ምንድነው ? ክፍል ሰባት 3ኛ) ምልክታዊ ትዕይንቶች እና እንቅስቃሴን የሚፈጥር ኃይል ያለው ትዕይንት Symbolic View and The Dynamic View

የመልእክት ርዕስ የሰዎችን ሥራም ሆነ የሥራ ጅማሬን ማወቅ ልታዋርደውም ጀመረች ኃይሉም ከእርሱ ሄደ (መሣፍንት 16 ፥ 9 ) ክፍል አንድ

የጌታ እራት ክፍል ሦስት