ትምህርት ሁለት እግዚአብሔር የማጣርያ ጊዜ አለው የትምህርቱ ዋና ዋና ሃሳቦች በዚህ የትምህርት ሁለት ክፍለ ጊዜ የምንመለከተው በዳዊትና በኦርዮ ቤት መካከል እግዚአብሔር ያደረገውን ማጣርያ ነው በዚህ ውስጥ ለማጣርያነት የተጠቀመበት ነቢዩ ናታንን ነው ስለዚህም ነቢዩ ናታን ጥበብ በተሞላበት የምሳሌ ቃል ወደ ዳዊት ከቀረበ በኋላ ዳዊት በገዛ አንደበቱ ተቆጥቶ እንዲህ ያደረገ ሰው ሞት ይገባዋል በማለት ፍርድ ሰጠ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ነቢዩ ናታን ያለምንም ማንገራገርና ማመንታት ያ ሰው አንተ ነህ ያለው ከዚያ በኋላም አቃለኸኛልና የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሖን ዘንድ ወስደሃልና ከቤትሕ ሰይፍ አይርቅም አለው ወገኖቼ እግዚአብሔር ጣልቃ ሲገባ ሰዎች ምንም ዓይነት ሰዎች ይሁኑ ራሳቸውን መደበቅም ይሁን ከራሳቸው መደበቅ አይችሉም የእግዚአብሔር ማጣርያ ካሉበት ነገር ውስጥ ፈልፍሎ ያወጣቸዋል ለዚህ የሚበጀው ነገር ወይም መፍትሔው ታድያ በእግዚአብሔር ማጣርያ ውስጥ ገብተው ሳይቀሉ ወይንም ያ ሰው አንተ ነህ ሳይባሉ ቶሎ በጊዜ ራስን ከተደበቁበት ወይም ከደበቁበት ነገር አወጥቶ ያ ሰው እኔ ነኝ በማለት ለንስሐና በሕይወት ለሚመጣ ለውጥ ይህንኑ ማንነት አሳልፎ መስጠት አዋቂነት ነው ሐዋርያው ጳውሎስ ማንም ሳይለው በሰዎች በኩልም ኃጢአተኛውና አሳዳጁ አንተ ነህ ሳይባል ከኃጢአተኞችም ዋናው እኔ ነኝ አለ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁ ምሕረትን አገኘሁ በማለት ተናገረ 1ኛ ጢሞቴዎስ 1 ፥ 13 ታድያ አንዳንድ ጊዜ በሰራነው በደል አንተ ነህ እስክንባል መጠበቅ የለብንም ጥፋት እንደሰራን ገብቶን ከሆነ ማለት ያለብን እንደ ጳውሎስ ከኃጢአተኞችም ዋናው እኔ ነኝ ነው ያኔ ጌታ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ስለሆነ የትኛውንም የተላለፍንበትን ኃጢአት ይቅር ይላል ሁለተኛው ሃሳብ በመርዶክዮስና በሐማ መካከል እግዚአብሔር የሕይወት ማጣርያ ሊያደርግ የተጠቀመበት መንገድ ነው መጠቀምያም ያደረጋት ለንግስትነት የቀረበችውን አስቴርን ነው አስቴር ግብዣ አድርጋ ንጉስ አርጤቅሲስንና ሐማን ወደ ግብዣ ከጠራች በኋላ ሐማ ባለ ማስተዋል አንድ ነገር ተናገረ ንግሥቲቱ ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ማንንም አልጠራችም ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ ነገር ግን አይሁዳዊ መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንም አይጠቅምም አለ ከዚያ በኋላ ነው በዘመዶቹ አነሳሽነት መርዶክዮስን ለማስገደል ግንዱን አስደረገ የሚለን ይህ እንግዲህ የሐማ ትልቁ ሞኝነት እና አላዋቂነቱ ነው ግብዣዎች ሁሉ አንዳንድ ጊዜ መልካም ናቸው ልንል ብንችልም ነገር ግን እግዚአብሔር በአስቴር በኩል ለንጉስ አርጤቅሲስና ለሐማ ያዘጋጀው ግብዣ የሐማን ማንነት ከመርዶክዮስ ይልቅ ለይቶ ለማወቅ የተዘጋጀ የእግዚአብሔር የማጣርያ ግብዣ ነው መጽሐፈ አስቴር 5 ፥ 12 _ ፍጻሜ ፣ መጽሐፈ አስቴር ምዕራፍ 6 ፣ ምዕራፍ 7 በሙሉ እናንብብ ታድያ በዚህ ግብዣ ላይ ሐማ እንዳለውና እንደፎከረው ተደስቶ ወይም ጥቅም አግኝቶ ግብዣው የተጠናቀቀ አይደለም ግብዣው የተጠናቀቀው ወይም የተደመደመው ሐማ ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ እንዲሰቀል ተበይኖ ፣ ሐማም ተሰቅሎ ፣ የንጉሡም ቁጣ ከሐማ መሰቀል የተነሳ በርዶ ነው አንዳንድ ግብዣዎች እንግዲህ ሐማ እንደጠበቃቸው ዓይነት ግብዣዎች ሳይሆኑ ቀርተው እና በምትኩም የእግዚአብሔርን ጽኑ የሕይወት ማጣርያን አምጥተው ይጠናቀቃሉ ለዚህም ነው መጽሐፍቅዱሳችን ሐማንም ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሰቀሉት በዚያም ጊዜ የንጉሡ ቁጣ በረደ ሲል የዘገበልን ከዚህም ሌላ ሐማ ለራሱ ባሰበው ፈረስ መርዶክዮስን ያስቀመጠ ፣ ለራሱ ያሰበውን ዘውድ ለመርዶክዮስ የጫነ ለራሱ ያሰበውን ልብሰ መንግሥት መርዶክዮስን ያለበሰ በአንጻሩ ደግሞ ለመርዶክዮስ ሞት ባዘጋጀው ግንድ ራሱ የተሰቀለ ነበረ የእግዚአብሔር የማጣርያ ጊዜ ሲመጣ እንግዲህ ዛሬም እንዲሁ ነው ከእኔ ወዲያ ስንል ለራሳችን ያመቻቸነው ለሌሎች ይሆናል ለነገሌ መጥፊያ ይሆናል ስንል ያወሳሰብነው ራሳችንን ያጠፋል ስለዚህ እግዚአብሔር ከዚህ የተሳሳተ ክፉ ሥራ እና እኩይ ተግባር ይጠብቀን የተወደዳችሁ ቅዱሳን የትምህርት ሁለት ሃሳብ በጣም ሰፊ ነው ነገር ግን ከዚህ ሌላ በውስጡ በቪዲዮ የተለቀቁ ብዙ የመጽሐፍቅዱስ ክፍሎች ያሉበት ማብራርያዎች አሉ እና በመቀጠል እንደሚከተለው በዚሁ ቪዲዮ የተለቀቁትን መልዕክቶች እየገባችሁ በመስማት ይበልጥ በስፋት መከታተል የምትችሉ መሆናችሁን በጌታ ፍቅር ለማሳሰብ እወዳለሁ ጌታ እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ አሜን

Comments

Popular posts from this blog

የጌታ እራት ዛሬ ለእኛ ምንድነው ? ክፍል ሰባት 3ኛ) ምልክታዊ ትዕይንቶች እና እንቅስቃሴን የሚፈጥር ኃይል ያለው ትዕይንት Symbolic View and The Dynamic View

የመልእክት ርዕስ የሰዎችን ሥራም ሆነ የሥራ ጅማሬን ማወቅ ልታዋርደውም ጀመረች ኃይሉም ከእርሱ ሄደ (መሣፍንት 16 ፥ 9 ) ክፍል አንድ

የጌታ እራት ክፍል ሦስት